ድር ቢያብር

አንበሳ ያስር እንዲሉ ሲተርኩ
በቁምነገር ሲተቹና ሲማርኩ፣
ታዲያ የዚህ አገር ሰው መች አጤነው
የወትሮ ሰዎች ስልታቸው ስላልገባው
በውሉ መተባበር ሲያቅተው።
አንበሳ የአውሬዎች ኃያል ንጉሥ ሆኖ
በጫካው ሁሉ ተዘዋውሮ ሥራውን ሁሉ
አጠናቆ አከናውኖ፣
በጣም ጉልበተኛ ሆኖ ሲያስፈራ
በድር ተጠምዶ ሲታሰርና ሲገራ፣
አባባሉ ግን ዕውነቱ
የአነጋገሩ ጥረቱ፣
ሕብረትን አጉልቶ ለማሳየት
ሥረ መሠረቱን አንጸባርቆ ለመለየት።
ለምን ይሆን የኛ ሰው ሕብረት ያጣው
ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ
መለያየቱን የመረጠው።
ትክክል የሚያስቡ ሰዎች ተባብረው
አብረው ለመሥራት ጥርጊያውን አሳምረው፣
ታላላቅ ሥራዎችን ለማከናወን ሲችሉ
ችላ በማለት ጊዜያቸውን ሲያቃጥሉ፣
ምኑን ብሎ ነው አንበሳው የታሠረ
መተግበር የነበረበት ወደኋላ እየቀረ።
የአገሩን ሰዎች እንደገና ምከሯቸው
መተባበር አስፈላጊ ነው በሏቸው፣
ለአገር ለትውልድ ሆኖ ቋሚ
መሠረታዊ ሃውልት ጠቃሚ
ኃያል የነበረውን እንኳን የሚገራ
መብትን አስጠባቂ የሚያኮራ።
ይህን ሁኔታ ሳንገነዘብ ከቀረን
ዕድገታችንን በአስር እጥፍ እንገታለን፣
ያለ ሁሉ አቅማችንን አስተባብረን ብንሠራ
ብዙ ችግሮቻችንን አጥፍተን ስናባራ፣
በሕብረታችን ጥሩ ኑሮን ገንብተን
ለልጆቻችንም መልካም ዕድል እንፈጥራለን።
እግዜር ይስጥልኝ።
ዓለማየሁ አስፋው

Share This Post!